A

Addis

ዜና

October 30, 2024

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የመመልመል ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን የሚደነግግ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ቀረበ

Politic

By

ሲሳይ ሳህሉ

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ለቦርድ ተሰጥቶ የነበረው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የመመልመል ሥልጣን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

ረቂቅ ሕጉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው፣ ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ነው፡፡

በ2013 ዓ.ም. ፀድቆ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዕጬ ዋና ዳይሬክተር በመገናኛ ብዙኃን ቦርድ ተመልምሎ፣ በመንግሥት አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሰየም ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ ሕግ፣ ሹመቱ የሌሎች አቻ ተቋማትን ተሞክሮና ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ አንፃር እንዲሻሻል ታስቦ መደረጉን ያስረዳል፡፡

የማሻሻያው አስፈላጊነት በሥራ ላይ ባለው ሕግ የቦርድ አሰያየምና አወቃቀር የተንዛዛና ረዥም ሒደትን የሚከተል በመሆኑ፣ ከዘርፉ ተለዋዋጭ ሁኔታ አንፃር አብሮ የማይሄድና የባለሥልጣኑን መደበኛ ተልዕኮዎች አስቻይ ውሳኔዎችን ከመስጠት አኳያ የመፈጸም አቅሙን የሚያስተጓጉል መሆኑ ታስቦበት እንደሆነ በረቂቁ ተገልጿል፡፡

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የተካተተው የቦርድ አባላት ስብጥር፣ ከባለሥልጣኑ የቁጥጥር ሚና ጋር በተያያዘ የጥቅም ግጭቶች የሚፈጥር ሆኖ መገኘቱ እንደ ክፍተት መታየቱ ተመላክቷል፡፡

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የቦርድ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ ያልሆኑ ተብሎ ቢደነገግም፣ በማሻሻያ ረቂቁ የቦርድ አባላት ለመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ቅርበትና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ አካላትና የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ከባድ ቅጣት ወይም መሰረዝ የሚያስከትሉ የተመለከቱ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ የቦርድ ኃላፊነት የነበረ ሲሆን፣ በተሻሻለው ረቂቅ ሕግ ለባለሥልጣኑ ተሰጥቷል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶበት ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴ በመራው በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል አወቀ አዘምየ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የቦርድ አባላት ከሚመረጡባቸው መሥፈርቶች አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ ያልሆኑ በሚል የተቀመጠ ቢሆንም፣ በቀረበው ረቂቅ ሕግ ግን ይህ መሥፈርት ለምን ተሻሻለ ሲሉ ጥያቄ አቀርበዋል፡፡

‹‹ይህንን አንቀጽ መሰረዝ ማለት የሚዲያ ገለልተኝነትን አደጋ ውስጥ የሚከትና በተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እንዲተኩ የሚያደርግ፣ የሚዲያ ምኅዳሩን የሚያጠብና ከሕዝብ ሀብትነት ወደ አንድ ፓርቲ የሚወስድ በመሆኑ ማብራሪያ ይሰጠን፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ሌላው የኢዜማ አባል አብርሃም በርታ (ዶ/ር)፣ ከገለልተኛነት ጋር በተያያዘ አዋጁ ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የቦርድ አባል አይሆንም ቢልም፣ በተሻሻለው ረቂቅ ግን እንዲወጣ መደረጉ ትክክል ስላልሆነ፣ በቀጣይ ተስተካክሎ እንዲቀርቡ አሳስበዋል፡፡ የቀረቡትን ጥያቄዎች የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲወያይባቸው ተመርቶለታል፡፡

Comments

No comments yet. Be the first to leave a comment!

Leave a Comment

Related Posts

Subscribe

You must accept the terms to subscribe.

© Copyright 2025 Addis News. All rights reserved.