November 06, 2024
በጋዜጣዉ ሪፓርተር
ባሳለፍነው ሳምንት ከተከሰቱና ዓለም አቀፍ ትኩረት ከሳቡ ዓበይት ክንዋኔዎች መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩሲያ ውስጥ ልምምድ ማድረጋቸውና ኩርስክ በምትሰኝ ዩክሬንን የምታዋስን ግዛት መሥፈራቸው ይገኙበታል፡፡ በተያያዘም ሰሜን ኮሪያ ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ የቻለ ባለስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፏ ሌላ አዲስ ውጥረት የፈጠረ ጉዳይ ነበር፡፡
የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ ምድር ልምምድ ማድረጋቸውን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአሜሪካ ልዑክ ሮበርት ውድ ዛቻ በቀላቀለ ድምፀት ነበር ‹‹በኮፈን ተጠቅልለው ይመለሷታል፤›› ሲሉ የተደመጡት፡፡
እንደ ዋሽንግተን ከሆነ ፒዮንግያንግ ከሩሲያ ጎን ተሠልፈው የሚዋጉ 10,000 ወታደሮቿን ወደ ሩሲያ ልካለች፡፡ ዩክሬን ደግሞ ቁጥሩን ከፍ በማድረግ ከሰሜን ኮሪያ ሩሲያ ውስጥ የሠፈሩ ወታደሮች 12,000 ይደርሳሉ ብላለች፡፡ ከእነዚህም 8,000 ያህሉ በዩክሬን ድንበር በምትገኘው የሩሲያ ግዛት ኩርስክ መሥፈራቸውን ከዋሽንግተን የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
‹‹ጉዳዩ እጅግ አሳስቦናል›› የሚሉት የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትሮች የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን እንደሚሉት፣ ሁኔታው ‹‹በሩሲያ ወረራ›› ምክንያት እ.ኤ.አ. በ2022 ፌብሩዋሪ በዩክሬን ውስጥ የተጀመረውን ወታደራዊ ግጭት ወደ ከፍተኛ ጡዘት ይወስዳል፡፡ ‹‹ወታደሮቻቸውን ከሩሲያ ምድር እንዲያስወጡ አሳስባለሁ፤›› ሲሉም ሎይድ ኦስቲን ባለፈው ሳምንት ከፔንታጎን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የፒዮንግያንግ ኃይሎች ዩክሬንን የሚያጠቁ ከሆነ የአሜሪካ ጦር ‹‹ሕጋዊ የጦርነት ዒላማ›› ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ሮበርት ውድ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባም ‹‹ሊቀመንበር ኪም ጆንግ ኡን እንደዚያ ካለ አደጋና ደንታ ቢስነት ራሳቸውን እንዲቆጥቡ እመክራለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ሞስኮ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ዩክሬን ውስጥ በምታደርገው ጦርነት የማሰማራቷን ውጥን እንደምትገፋበት ሎይድ ኦስቲን ይናገራሉ፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፣ ዩክሬን ውስጥ እያደረጉ ላሉት ዘመቻ የጦር አሠላለፍና ታክቲክ ምክር ከማንም እንደማይቀበሉ ተናግረዋል፡፡ የሰሜን ኮሪያ ጦር አባላት በሩሲያ መኖራቸውን ባይክዱም፣ በዩክሬን ይሰማራሉ ለሚለው የአሜሪካ ስሞታ ግን የሰጡት ምላሽ የለም፡፡
ዘጋርዲያን እንደዘገበው፣ ሩሲያ በሚቀጥሉት በርካታ ሳምንታት 10,000 የሚሆኑ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ዩክሬን ውስጥ ለምታደርገው ዘመቻ እንዲሠለፉ አሠልጥና ታሰማራለች፡፡
ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የምታደርጋቸው ወታደራዊ ግንኙነቶች ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር የሚጋጩ እንዳልሆነ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያ ቋሚ መልዕክተኛ ለፀጥታው ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በተደረገው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ፣ ቫሲሊ ነበንዚያ እንደተናገሩት፣ ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ያላት ወታደራዊና ሌሎች ግንኙነቶች የዓለም አቀፍ ሕጎችን ካለመጣሳቸውም ባሻገር ሦስተኛ አገር ላይ ያነጣጠረ አይደለም፡፡
የአሜሪካው መከላከያ ምክር ቤት ፔንታጎን የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚያሳይ ያለውን ተንቀሳቃሽ ምሥል የለቀቀ ሲሆን፣ ክስተቱ በሩሲያና በአሜሪካ መካከል አዲስ ፍጥጫ ፈጥሯል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለኒስኪ በአጋጣሚው የተጠናከረ ድጋፍ ከአጋር አገሮች ለመሰብሰብ ጥሪ አድርገዋል፡፡ የሩሲያ ጦር በምሥራቅ ዩክሬን የሚያደርገው የሰመረ ግስጋሴ በቀጠለበት ወቅት፣ ዘለኒስኪ ለዋሽንግተንና አጋሮቻቸው ‹‹የድል ውጥን›› ያሉትን በማቅረብ የሚደረግላቸው የጦር ድጋፍ እንዲጨምር ቢጥሩም፣ የተሳካላቸው አይመስልም፡፡
አሜሪካ በምርጫ ፉክክር ሒደት ጡፋለች፣ አውሮፓውያን ደግሞ ቀድሞ ለዩክሬን ያዥጎደጎዷቸው የጦር ትጥቆች ዒላማቸውን በሚጠበቀው ልክ ባለመምታታቸው ተጨማሪ ዕርዳታ ለማድረግ የሚቻኮሉ ሆነው አልተገኙም፡፡ ስለዚህ ነው ዘለኒስኪ ይህን የሰሜን ኮሪያ ጦር በኩርስክ የመከተም ጉዳይ አፅንኦት ሰጥተው፣ ምዕራባውያንን ለመኮርኮርና የጦር ድጋፍ ለማጋበስ እየጣሩ የሚገኙት፡፡
እንደ ፖለቲካና ወታደራዊ ተንታኞች፣ ዩክሬን አሜሪካ ሠራሽ የሆኑ የረዥም ርቀት ከባድ ሚሳይሎቿን ተጠቅማ ሞስኮን ጨምሮ የሩሲያን መካከለኛ ግዛቶች እንድታጠቃ ለዩክሬን ፈቃድ ሳትሰጥ ቆይታለች፡፡ ጉዳዩ የአሜሪካ ምርጫን ውጤት ይጠብቃል ይላሉ ተንታኞቹ፡፡ ዴሞክራቷ ካማላ ሃሪስ ካሸነፉ፣ ዩክሬን ፈገግ ትላለች፣ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ አሸናፊ ከሆኑ ደግሞ ዩክሬን ጥይት አጠር ትሆናለች፡፡
እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 24 ቀን 2022 ነበር የሩሲያ ጦር የዩክሬንን ምድር ዘልቆ የገባው፡፡ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ዩክሬንን አባል ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ካስታወቀ በኋላ፣ ሩሲያ ከ2021 ጀምሮ ጦሯን ወደ ዶንባስ ድንበር አካባቢዎች ስታከማችና ኔቶ ከድርጊቱ እንዲታቀብ የቀደሙ ስምምነቶችን በመጥቀስ ስትወተውት ቆይታ ነበር፡፡ ኔቶ የሩሲያን ተደጋጋሚ ጥሪ ቸል ከማለት አልፎ፣ ሩሲያ በዩክሬን ጦር የምታዘጋጅ ከሆነ ዩክሬንን በጦር እንደሚደገፉ ይገልጹ ነበር፡፡
ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር ‹‹አሳካለሁ›› ካለቻቸው አጀንዳዎች አንዱ ‹‹በዩክሬን ፋሽስታዊ አገዛዝ ሥር የወደቁ የዶንባስ ነዋሪዎችን እታደጋለሁ፤›› የሚል ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 2022 ዶንባስ ግዛት ውስጥ ባሉ ዶኔትስክና ሉሃንስክ ብሎም በኬህርሶንና ዛፖሪዢያ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ድምፅ እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በውጤቱም እነዚህ ግዛቶች በሩሲያ አስተዳደር ሲወድቁ፣ ከሰሜን ኮሪያ በስተቀር ውጤቱን በኦፊሴል የተቀበለ አገር የለም፡፡ አሜሪካና አውሮፓውያን ግን አጥብቀው ኮንነውታል፡፡
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት አዲስ መልክ እየያዘ የመምጣት አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ የሰሜን ኮሪያ ጦር አባላት ወደ ዩክሬን ዘልቀው በመግባት ከተኮሱ፣ ግጭቱ በኃያላኑ አገሮች መካከል የመሆን ዕድል እንደሚኖረው አንዳንድ ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ባለፈው ሳምንት ሰሜን ኮሪያ የምዕራቡን ዓለም ትርታ የጨመረ የባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ ያደረገችው፡፡
በዕለተ ሐሙስ በሰሜን ኮሪያ የተተኮሰው አኅጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ሲሆን፣ ለ87 ደቂቃዎች መምዘግዘግ ችሏል፡፡ ዓምና በዲሴምበር 2023 ያስወነጨፈችው ሚሳይል የጉዞ ቆይታው 73 ደቂቃዎች እንደነበር ይታወሳል፡፡
የጃፓን መንግሥት እንዳለው፣ ይኼ በዓይነቱ አዲስ የሆነ የሰሜን ኮሪያ ባለስቲክ ሚሳይል 1000 ኪሎ ሜትር የተጓዘ ሲሆን፣ ከፍታው እስከ 7,000 ኪሎ ሜትር ዘልቋል፡፡ ይህ በምሥራቅ አቅጣጫ የተተኮሰ ሚሳይል በመጨረሻም የ‹‹ጃፓን ባህር›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰጥሞ እንዲፈነዳ ተደርጓል፡፡
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን በአገሪቱ ቴሊቪዥን ቀርበው፣ ‹‹ይህ የሙከራ እቶን በቅርቡ ሆን ብለው ቀጣናውን ውጥረት ውስጥ ለማስገባት ጥረት ለሚያደርጉት ባላንጦቻችን መልስ የሚሆን ተገቢ የሆነ ወታደራዊ ዕርምጃ ነው፤›› ሲሉ የሚሳይሉን የተሳካ ሙከራ አሞካሽተዋል፡፡
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን እሑድ ዕለት የጋራ ጦር ልምምድ አድርገዋል፡፡ ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ባለፈው ሐሙስ በሰሜን ኮሪያ የተተኮሰው ህዋሶንግ-19 የተሰኘ ባሊስቲክ ሚሳይል ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደም ከተኮሰቻቸው ሁሉ የጎላ ብቃት ያሳየ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰንዝራለች፡፡ እሑድ ዕለት በተደረገ የሩሲያ የድሮኖች ጥቃት ኪየቭ ውስጥ ባሉ መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ሆኖም የኪየቭ አስተዳዳሪ በጥቃቱ የሞተ ሰው የለም ሲሉ ከመደመጣቸው ባሻገር ሁሉም ድሮኖች ተመትተው መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ፍራንስ 24 እንደዘገበው፣ ቅዳሜ ለእሑድ ሌሊት በተደረጉ የድሮን ድብደባዎች በኪየቭ ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሩሲያ የድሮን ጥቃቶች በኪየቭ የተለያዩ አካባቢዎች ውድመት ያደረሱ ሲሆን፣ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችም አሉ ሲሉ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለኒስኪ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሩሲያና አጋሮቿ ላይ ጫናዎች በማድረግ ብቻ ማሳረፍ እንደማይቻል ማረጋገጫ ነው፤›› ሲሉም የሩሲያን አዲስ የድሮን ጥቃት ገልጸውታል፡፡
ፍራንስ 24 የዩክሬንን አየር ኃይል ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ከሩሲያ ከተላኩ 71 ድሮኖች 39 ያህሉ ተመትተው ወድቀዋል፡፡ ድሮኖቹ ያተኮሩት ኪየቭን፣ ኪሮቮግራድንና ፖልታቫ የተሰኙ ክልሎችን ነው፡፡ የኪየቭ ባለሥልጣንን ጠቅሶም፣ የ82 ዓመት ሴት አዛውንት በወደቀ ድሮን ፍንጣሪ የራስ ቅል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ ሕንፃዎች፣ ሆስፒታሎችና የፖሊስ ጣቢያዎች ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል እንደሚገኙበት ዘግቧል፡፡
የኪየቭ ከተማ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ ሴርሂ ፓፕኮ እንዳሉት፣ ለአምስት ከግማሽ ሰዓታት የዩክሬን አየር መቃወሚያዎች የሩሲያ ድሮኖችን በመጣል ተጠምደው አድረዋል፡፡ የድሮን ስብርባሪዎች ሆሎኪቪስኪና ቼቩቼንኪቩስኪ ሠፈሮች ወዳድቀው ተስተውለዋል ሲል የዘገበው ደግሞ የቱርኩ ዜና ወኪል አናዶሉ ነው፡፡
የዜና አውታሩ ፓፕኮን በመጥቀስ እንደዘገበው፣ የድሮን ውድቅዳቂ አካላት መንገዶችን አርሰዋል፣ የመንገድ መብራት ምሰሶዎችን ገነዳድሰዋል፣ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ከሩሲያ በምትዋሰነው የዩክሬን ሱሚ ክልል ላይ በተደረገው የሩሲያ ድሮን ድብደባ ደግሞ የከተማና የገጠር መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡
No comments yet. Be the first to leave a comment!
Silence Between the Lines
May 03, 2025
A Looming Hunger Crisis: Malnutrition Rises Amid Supply Disruptions in Ethiopia
April 26, 2025
Markets in Slump Ahead of Easter Celebrations
April 19, 2025
Reviving a Vanishing Tongue: The Return of Ge’ez
April 12, 2025
Ethiopia Reads: A Grassroots Revolution in Literacy
April 05, 2025
Trapped between poverty and peril: Ethiopia’s struggle to curb youth migration
March 29, 2025
Silenced by Techno-patriarchy
February 28, 2025
From Catcalling to Femicide: The Violence We’ve Learned to Survive
December 09, 2024
Ethiopia’s Fashion Stars Shine in Creative DNA: Ethiopia 2.0
December 03, 2024
Betrayed on Every Front: How the Law, Society, and Police Failed Tsega Belachew
November 19, 2024
New Education Bill Proposes No Student Ranking Until Grade 6: A Shift Towards Inclusive Learning
October 30, 2024
© Copyright 2025 Addis News. All rights reserved.