A

Addis

ዓለም

October 23, 2024

እስራኤል ከሃማስና ሂዝቦላህ የገባችበት ጦርነት ወደ ኢራን ያመራ ይሆን?

Politic

By

ምሕረት ሞገስ

ሃማስ ከጋዛ ወደ እስራኤል በተኮሳቸው ከሦስት ሺሕ የሚልቁ ሮኬቶች የተጀመረው የእስራኤል ጋዛ ፍልስጤም ጦርነት፣ ዛሬ ላይ አድማሱን አስፍቶ ወደ ሊባኖስ ሂዝቦላህ ብሎም ሶሪያ ደርሷል፡፡

ከሮኬቶች ጥቃት፣ ከእግረኛ ጦርነት፣  ከተዋጊ ጀቶች የቦንብ ውርጅብኝ አልፎም አሁን ላይ በእስራኤልና አሜሪካ ውስጥ አይደፈሬ የተባለ ሚስጥር እስከመሹለክ ተወሳስቧል፡፡

እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2023 በእስራኤልና ሃማስ መካከል ለተጀመረው ጦርነትና አጠቃላይ ለመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም መደፍረስ ከኋላ ኢራን አለች የምትለው እስራኤል፣ በቀጣይ ኢራን ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ስለማቀዷ የተሰናዳው ሰነድ አፈትልኮ መውጣቱን የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ጆን ኪርባይ ተናግረዋል፡፡

ሰነዱ የወጣው ተጠልፎ ይሁን አፈትልኮ ግልጽ ያላደረጉት ቃል አቀባዩ፣ ሰነዱ እስራኤል ኢራን ከሁለት ሳምንታት በፊት ለሰነዘረችባት የሚሳይል ጥቃት አፀፋ ለመስጠት ስለምታደርገው ወታደራዊ ዝግጅት ዕቅድና የአሜሪካን ዳሰሳ ያካተተም ነበር፡፡

ጥብቅ ሚስጥር ተብሎ የተዘጋጀው ሰነድ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የካናዳ፣ የኒውዚላንድና የአውስትራሊያ ጥምር ለሆነው ደኅንነት ክፍል የተላከም ነበር፡፡

ይህንኑ ተከትሎ ለሚሰነዘርባት ጥቃት ምላሽ እንደምትሰጥ ኢራን ስታስታውቅ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ደግሞ ትናንት ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር ለመምከር ቴልአቪቭ ገብተዋል፡፡

እስራኤል በኢራን ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ የመውሰዷ ሁኔታ ባየለበትና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የተደረጉ ጥረቶች ሁሉ ይሁንታ ባጡበት የብሊንከን ቴልአቪብ መግባት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተስፋፋ የመጣውን ጦርነት ለማስቆም የተጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማጠናከር እንደሆነ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

እስራኤልና ሃማስ ከዓመት በፊት የጀመሩትን ጦርነት በአንድ ወገን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ፣ በሌላ በኩል ለእስራኤል የጦርና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የምትሳተፈው አሜሪካ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ እስራኤል ስትልክ የአሁኑ ለ11ኛ ጊዜ ነው፡፡

የአሁኑ የብሊንከን ጉዞ በተለይ እስራኤል በኢራን ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ማቀዷ አፈትልኮ ከወጣበትና እስራኤል በሊባኖስና በጋዛ ፍልስጤም እየወሰደች ያለው ወታደራዊ ዕርምጃ ባየለበት ነው፡፡

እስራኤል በሊባኖስና በጋዛ የምታደርገው ወታደራዊ ዕርምጃ ቢያይልም፣ በእስራኤል ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችም እየጨመሩ ነው፡፡ ብሊንከን ቴልአቪቭ ከመድረሳቸው ሰዓታት አስቀድሞም ሂዝቦላህ ወደ ከተማዋ ሮኬት መተኮሱ ተሰምቷል፡፡ እስራኤላውያን የፍንዳታ ድምጾች መስማታቸውን ሲገልጹ፣ መንግስት ደግሞ ‹‹ብዙዎቹን አክሽፌያለሁ፣ የቀሩትም ባዶ ስፍራ ላይ አርፈዋል›› ብሏል፡፡

እስራኤል ከፍልስጤም ጋዛ የገጠመችው ጦርነት ሳያባራ በሊባኖስ ሂዝቦላህ ላይ የጀመረችው ጦርነት በሊባኖስ ብቻ የሚያቆም ሳይሆን፣ የሂዝቦላህ አባላት ይገኙባቸዋል በሚባሉ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሙሉ እንደሚሆን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ኤቢሲ ዘግቧል፡፡

እስራኤል በሂዝቦላህና ሃማስ ላይ በምትወስደው ዕርምጃ ሆስፒታሎችን ጨምሮ ማኅበራዊ ተቋማት ሁሉ እየወደሙ ሲሆን፣ በተለይ ጋዛ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይራለች፡፡

ከ42 ሺሕ የሚልቁ ዜጎችም ተገድለዋል፡፡ ነዋሪዎቿ ለሰብዓዊ ቀውስ ተዳርገዋል፡፡ ከሃማስና ሂዝቦላህ በኩል በእስራኤል የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሰላማዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ቢሉም፣ እስራኤል ዒላማዎቿ የቡድኖቹ መሸሸጊያ፣ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ክምችት ያሉባቸውና ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው ስትል ትገልጻለች፡፡ ከእስራኤል ወገንም ወታደሮችንና አዛዦችን ጨምሮ ከ1100 የሚልቁ ተገድለዋል፡፡

ከሃማስና ሂዝቦላህ የሚወነጨፉባትን ሮኬቶች በአብዛኛው ስትመክት የቆየችው እስራኤልም፣ ሂዝቦላህ በሰሜን እስራኤል የሰነዘረባትን ጥቃት ተከትላ በቴልአቪቭ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በፍልስጤም ከሚደርሱ ቁሳዊ ጉዳቶች በተጨማሪ ከጋዛ ሰዎች እንዲፈናቀሉና ሥፍራውን ለቀው መጠለያ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የሚደረግላቸው ድጋፍም እየተስተጓጎለ ነው፡፡ በጋዛ ፍልስጤማውያን ከቀያቸው ሲሰደዱ፣ አይሁዶች በጋዛ መስፈር አለባቸው የሚሉ እስራኤላውያን ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡

ሲኤንኤን በጋዛ አይሁዶች እንዲሰፍሩ ጥሪ የቀረበበትን ዝግጅት አስመልክቶ እንደዘገበው፣ የእስራኤል ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀኝ ዘመም የእስራኤል ወትዋቾች በጋዛ ድንበር አካባቢ በተዘጋጀ መድረክ በመኘት መንግሥት በጋዛ አይሁዶችን እንዲያሰፍር፣ ከጋዛ ፍልስጤማውያን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እስራኤል ከሃማስ ጋር ጦርነት ከገጠመች ዓመት ቢሆንም፣ በሊባኖስ ሂዝቦላህ ላይ የከፈተችውን መጠነ ሰፊ ጥቃት የጀመረችው በቅርቡ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ ዒላማዎችን መምታቷን እያስታወቀች ትገኛለች፡፡

ከሂዞቦላህ ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ባንክን ጨምሮ ሆስፒታሎችና ሌሎች ተቋማት የአየር ጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡ በሊባኖስ ጥቃት ከጀመረችበት ከመስከረም 2017 ዓ.ም. ማገባደጃ ወዲህም 3200 ዒላማዎችን መትቻለሁ ብላለች፡፡

ሂዝቦላህ በበኩሉ በእስራኤልና በወታደሮቿ ላይ 31 ጥቃቶችን መፈጸሙን፣ ለዚህም ሮኬቶች፣ ሚሳየሎችና ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ጠቁሟል፡፡፡

የእስራኤል ጋዛ ፍልስጤም ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ኢራን ሁለት ቀጥተኛ የሚሳይል ጥቃቶችን በእስራኤል ላይ ስትፈጽም፣ እስራኤልም በኢራን በውትድርና ተቋማት ላይ አንድ የአፀፋ ምላሽ ሰጥታለች፡፡ በቅርቡ ከኢራን ለተሰነዘረባት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ማቀዷም ተሰምቷል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ይመጣ ዘንድ በእስራኤልና ፍልስጤም በኩል የሁለትዮሽ ስምምነት የሚደረግበት አካሄድ እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ፣ ሰላሙን ለማስፈን የመካከለኛው ምሥራቅና ምዕራባውያን የተሳተፉባቸው ውይይቶች፣ ቢደረጉም ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም፡፡

ኢራን በውክልና ከእስራኤል ጋር ታዋጋቸዋለች የሚባሉት ሃማስና ሂዝቦላህም ጥቃታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ እስራኤልም እነሱ ባሉበት ሁሉ ዕርምጃ ከመውሰድ አልቆጠብም ስትል አስታውቃለች፡፡

እስራኤል ውስጥ ከሚደርሱ ጥቃቶች ጀርባ አለች በመባል የምትወቀሰው ኢራን በበኩሏ፣ ለእስራኤል እንደማትተኛ እየገለጸች ነው፡፡ እስራኤል ከሃማስና ሂዝቦላህ ጋር የባችበት ጦርነት ወደ ኢራን ሊያመራ እንደሚችል ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን ሚሽን በበኩሉ፣ እስራኤል ኢራን ላይ ለመውሰድ ላቀደችው ወታደራዊ ጥቃት አሜሪካ ዘመናዊ መሣሪያዎች በማቅረብ ጣልቃ እንዳትገባ አስጠንቅቋል፡፡

Comments

No comments yet. Be the first to leave a comment!

Leave a Comment

Related Posts

Subscribe

You must accept the terms to subscribe.

© Copyright 2025 Addis News. All rights reserved.