October 16, 2024
በጋዜጣዉ ሪፓርተር
ከአራት ቀናት በፊት የሱዳን ጦር ኃይል ዋና ከተማዋን ካርቱምን መልሶ ለመቆጣጠር ባደረገው ማጥቃት፣ በከተማዋ ውስጥ ያለ ገበያ ከአየር በመደብደቡ 13 ሰዎች እንደሞቱና በርካቶች እንደቆሰሉ ተዘግቧል፡፡
በሱዳን ተፋላሚዎች መካከል የሚደረገው ጦርነት ተፋፍሞ በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ ወደ ቀጣናው ጦሯን እያስጠጋችና ቀስ በቀስ እግሯን እየተከተለች የምትገኘው ግብፅ በፍልሚያው ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጋለች የሚል ክስ ከአንደኛው ተፋላሚ ወገን ባለፈው ሳምንት ቀርቦባታል፡፡
ከኤፕሪል 15 ቀን 2023 እስካሁን ድረስ ለአንድ ዓመት ተኩል ሳያባራ የቀጠለው ጦርነት የተጀመረበት ዕለት ነበር፡፡ በታላቁ የረመዳን ፆም፡፡
በጄኔራል አብደልፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ኃይሎች፣ በጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) ከሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር የተማዘዘበት ዕለት፡፡
በእነዚህ ሁለት ፈርጣሞች እየተባባሰ ለዘለቀው ጦርነት መነሻው ሥልጣን፣ ብሎም ቁልፍ የኢኮኖሚ አውታሮችን በበላይነት መቆጣጠር መፈለግን የተመለከቱና ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህ የዘመኑ እጅግ አስከፊ በተባለለት የእርስ በርስ ጦርነት ከ15‚000 በላይ ሱዳናውያን ሲገደሉ፣ አሥር ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ ለስደት ተዳርገዋል፡፡
እነዚህ ሁለት ኃያላን የጦር አበጋዞች ኃይሎቻቸውን ክተት ከማለታቸው አስቀድሞ፣ አሁን እስር ላይ በሚገኙት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ትዕዛዝ ሥር የተሠለፉ ነበሩ፡፡ ቀድሞ ለበርካታ ዓመታት የጃንጃዊድ ሚሊሺያዎች በመባል የሚታወቁትን ዓረብ ቀመስ ሱዳናዊ ታጣቂዎችን በማሰባሰብ፣ በማሠልጠንና በማስታጠቅ፣ ከዚህ በመለስም ለመሪዎቻቸው መደበኛ ወታደራዊ ማዕረጎች በመስጠት ፈጥኖ ደራሽ ጦር ሲሉ ያቋቋሙት አል በሽር ነበሩ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን በዳርፉር የሚኖሩና ተገፍተናል የሚሉ ብሔረሰቦችን አመፅ ለመደፍጠጥ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. በ2019 ታላቅ የታሪክ ምፀት የተባለውን የዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ከአል ቡርሃን የሱዳን መደበኛ ጦር ኃይሎች ግንባር በመፍጠር፣ አል በሽርን ከሥልጣን አሽቀንጥሮ የጣለ መፈንቅለ መንግሥት ፈጸሙ፡፡
የሲቪል አገዛዝ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንበሩን እስኪረከብ በሚል ቀድሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ጸሐፊ የነበሩትን አብደላ ሃምዶክን የጊዜያዊ ሽግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ በጎ የሚመስል ጅምር፣ ብዙም ሳይቆይ የሁለቱ ጄኔራሎች እሰጥ አገባ እየተካረረ መጥቶ ሰላምና ለውጥ ፈላጊ ሱዳናውያንን አንገት በማስደፋት አገሪቱ ወደ ጦርነት አዘቅት ገባች፡፡
የእርስ በርስ ጦርነቱ ቀጥሎ ባለበት በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዘር ፍጅት ጉዳዮች ልሂቅ የሆኑት አለስ ዋኢሪሙ ንደሪቱ፣ ግጭቱ መቋጫ ወደ ሌለው የመጠቃቃት ዑደት መድረሱን ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ ተደምጠዋል፡፡ በአሥራ ስምንት ወራት የተጧጧፈ ግጭት በአሥር ሺዎች አልቀዋል፣ ከቀዬአቸው ከተፈናቀሉ አሥር ሚሊዮን ሱዳናውያን በተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዋል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በአጠቃላይ ቀጣናው ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት ተጋልጦ ባለበት ወቅት መሆኑ ሰብዓዊ ችግሩን ጥልቅና የተወሳሰበ አድርጎታል፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዳስታወቀው 18 ሚሊዮን ሱዳናውያን፣ ሰባት ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን እንዲሁም ሦስት ሚሊዮን ቻዳውያን በአጣዳፊ የምግብ ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡
እንደ ዘ ጋርዲያን ዘገባ ከሆነ ደግሞ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ (አሜሪካ)፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኢራን በሚያደርጉት ቀጣናዊ፣ ጂኦ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የማሳረፍ እንቅስቃሴ በሱዳን ውስጥ ያለውን ጦርነትና ውጥረት እንዲባባስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሱዳን ሲቪል መር የሆነ መንግሥት ቢመሠረት አክራሪ እስላምን ሊገዳደር ይችላል ከሚል ተስፋ መነሻነት፣ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታትን በማስተባበር በተመሠረተ ‹‹ቋድ›› የተሰኘ በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ኅብረት በሚመራ በሱዳን ተቀናቃኞች መሀከል የሰላም ድርድር ሒደት ተሳትፈዋል፡፡ ምዕራባውያን አገሮች ደግሞ በሱዳን የጦር መሪዎች ይሁንታ የተቸረውን በቀይ ባህር ላይ የሩሲያን ባህር ኃይል እግር የመትከል ጉዳይ ይፈሩታል፡፡ እስካሁን ይሁንታ ባታገኝም ኢራንም በሱዳን ባህር ላይ ኃይል እንዲኖራት ጠይቃለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ ሰሜን አፍሪካዊቷ የዓረብ አገር ግብፅ ጦሯን በሶማሊያ ወደብ በማራገፍ፣ በሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ እጇን ያስገባችው፡፡ ግብፅ በግልጽ የጄኔራል አል ቡርሃንን ቡድን ከመደገፍ ባለፈ በሱዳን ዋና ከተማ ተንሰራፍቶ በቆየው የጄኔራል ደጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃቶች እንዲፈጸም ቀጥተኛ ትብብር ማድረጓ ተዘግቧል፡፡ ይህን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር መሪ ያቀረቡባትን ክስ ግብፅ ከስድስት ቀናት በፊት በወጣ መግለጫ እንዳልፈጸመች አስተባብላለች፡፡
አልጄዚራ እንደዘገበው ካርቱምን መልሶ ለመያዝ የጄኔራል አል ቡርሃን ጦር በሚያደርገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ፣ ብሎም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሚያደርገው የካርቱም ይዞታውን የማስጠበቅ መከላከል በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ከመድረሱ ባሻገር፣ በአሁኑ ወቅት በመላው ካርቱም ትንሽም ቢሆን የጤና አገልግሎት ላለማቋረጥ እየተፍጨረጨረ የሚገኘው አንድ ሆስፒታል ብቻ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ሕመምተኞች ለሞት እንደሚዳረጉ የተሠጋ ሲሆን፣ በከተማይቱ ኮሌራ እየተስፋፋ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳንን በእስራኤልና በሐማስ ግጭት ቅንብብ ውስጥ ለመክተት የሚችል አንድ ሒደት በሚድል ኢስት ሞኒተር ተዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ድብደባ ጋብ ታደርግ ዘንድ ካስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሀል፣ በቅርቡ የተሰየሙትን ያህያ ሲንዋርን ጨምሮ የሐማስ የጦርና የፖለቲካ መሪዎች ወደ ሱዳን እንዲሰደዱ ማድረግ ይገኝበታል፡፡ ይህንን የእስራኤል ሐሳብ ኢዘት አል ሪስቅ የተባሉ የሐማስ አፈ ቀላጤ ‹‹አስቂኝ ቅዥት›› ብለውታል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሐማስ በፍልስጤም ግዛት ወራሪ ጠላትን እየተዋጋ ያለ ኃይል ነው፡፡
የሆነ ሆኖ የቀጣናዊ ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑ በርካቶች ለ18 ወራት ቀጥሎ ተባብሶ የዘለቀው የሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ተገቢው ዓለም አቀፍ ትኩረት አልተቸረውም ይላሉ፡፡
የስቲምሰን ማዕከል ተንታኝ ማይክል ከርቲን እንደሚሉት ከሆነ የዓለም ቀልብ በዩክሬንና በጋዛ ላይ ብቻ አተኩሮ ሳለ፣ በሱዳን ውስጥ እየተፈጸመ የቀጠለው የሰብዓዊ መብት ገፈፋ ብሎም የዘር ማጥራት ተባብሷል፡፡ ጦርነቱ ተጀምሮ አሥር ወራት እንዳለፉ በሰሜን ዳርፉር ዘምዘም በተሰኘ መጠለያ ካምፕ ውስጥ በየሰዓቱ አንድ ሕፃን ለሕልፈት ይዳረግ እንደነበር፣ ሜዲሲንስ ሳንፍሮንቴርስ የተባለ ግብረ ሰናይ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2024 ለሱዳን ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈለጋል ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጠቀሰው 4.1 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ የተገኘው 39 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው፡፡ የተገኘውን ያህል የሰብዓዊ ዕርዳታ እጅግ ከሚያስፈልጋቸው ሱዳናውያን ዘንድ ለማድረስ ከፍተኛ ችግር ይገጥመው እንደነበርም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊና የአስቸኳይ ዕርዳታ ድርጅት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትዝ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሱዳን ቀውስ በዓለም ካሉ እጅግ የከፉ ቀውሶች አንዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የተዘነጋው ጦርነት››፣ ‹‹የሁለት ጄኔራሎች ጦርነት››፣ እና ‹‹የውክልና ግጭት›› በሚል የዳቦ ስሞች የወጡለት የሱዳን የእርስ በርስ ዕልቂት በአስቸኳይ መቋጫ ካላገኘ አገሪቱ የማትወጣው የተባባሱ ቀውሶች ይጠብቋታል፣ እንደ ፖለቲካ ተንታኞች ከሆነ፡፡ አሁን በሚስተዋለው ሁኔታ ደግሞ ለቀውሱ መውጫ የታሰበለት አይመስልም፡፡
ከሁለቱ ዋና ተፋላሚዎች በተጨማሪ ላለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ብሔረሰቦች እንወክላለን የሚሉ ታጣቂዎች በዳርፉርና በብሉ ናይል ክልሎች የእርስ በርስ ውጊያ ተዋንያን ነበሩ፡፡
በርካታ የዓለም አቀፍ የሰላም ጥረቶች ሳይሳኩ የቀሩ ሲሆን፣ የውክልና ጥያቄዎችም የሰላምን ጥረት ከሚያደናቅፉ በርካታ ምክንያቶች ተጠቃሽ ነው፡፡ ለምሳሌ በጀንዋሪ አጋማሽ ኢጋድ ስብሰባውን እንዲቀላቀል ለደጋሎ ባስተላለፈው ጥሪ የተነሳ የሱዳን መንግሥት ከኢጋድ ጋር ያለውን ግንኙነት ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን አስታውቆ ነበር፡፡
ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ የክልል አቀፍ ድርጅቶች በሱዳን ተፋላሚዎች መካከል ሰላም ለማስፈን የሚያደርጉትን የተወሰኑ ጥረቶች እንኳ ቸል ብለዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዩክሬንና በጋዛ፣ ከቅርብ ጊዜ ደግሞ ከፍተኛ የዓለም ሥጋት ደቅኖ በሚገኘው የእስራኤልና የኢራን ፍጥጫ በማተኮሩ ነው ይላሉ ተንታኞች፡፡
የሆነ ሆኖ በሱዳን እየተባባሰ የሚገኘው ቀውስ ከቀጠለ ከባድ አካባቢያዊ ጦሶች እንደሚኖሩት ያስጠነቅቃሉ፣ ሰሚ ከተገኘ፡፡
No comments yet. Be the first to leave a comment!
Silence Between the Lines
May 03, 2025
A Looming Hunger Crisis: Malnutrition Rises Amid Supply Disruptions in Ethiopia
April 26, 2025
Markets in Slump Ahead of Easter Celebrations
April 19, 2025
Reviving a Vanishing Tongue: The Return of Ge’ez
April 12, 2025
Ethiopia Reads: A Grassroots Revolution in Literacy
April 05, 2025
Trapped between poverty and peril: Ethiopia’s struggle to curb youth migration
March 29, 2025
Silenced by Techno-patriarchy
February 28, 2025
From Catcalling to Femicide: The Violence We’ve Learned to Survive
December 09, 2024
Ethiopia’s Fashion Stars Shine in Creative DNA: Ethiopia 2.0
December 03, 2024
Betrayed on Every Front: How the Law, Society, and Police Failed Tsega Belachew
November 19, 2024
New Education Bill Proposes No Student Ranking Until Grade 6: A Shift Towards Inclusive Learning
October 30, 2024
© Copyright 2025 Addis News. All rights reserved.