A

Addis

ዜና

October 30, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገ በፓርላማ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ይሰጣሉ

Politic

By

ሲሳይ ሳህሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ነገ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚነሱላቸው ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጡ ታወቀ፡፡

በመስከረም 2017 ዓ.ም. መጨረሻ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የመጀመሪያ ስብሰባ፣ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት ታዬ አጽቀሥላሴ በመንግሥት የዘንድሮ ዕቅድ ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ የምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረገው አራተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከለትን የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ አፅድቋል፡፡

ሹመታቸው በምክር ቤቱ የፀደቀላቸው ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር፣ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ሆነው እንዲሾሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ በላኩት ደብዳቤ መሠረት ነው፡፡

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የቱሪዝም ሚኒስትር፣ እንዲሁም ወ/ሮ ሐና አርዓያ ሥላሴ የፍትሕ ሚኒስትር ያደረጓቸውን ተሿሚዎች ፓርላማው ተቀብሎ አፅድቋል፡፡

ይሁን እንጂ አሿሿሙና ለፓርላማው እንዲፀድቅ የቀረበበትን መንገድ በተመለከተ ከአባላቱ ጥያቄ ተነስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ አባል አቶ ባርጠማ ፈቃዱ ባነሱት ጥያቄ፣ የሁለቱ ሚኒስትሮች ሹመት ምክር ቤቱ ሦስተኛ የሥራ ዘመኑን ከመዘጋቱ በፊት በ2016 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ የተሰጠ ቢሆንም፣ እስካሁን ለፓርላማው አለመቅረቡ ከምክር ቤቱ አሠራርና ሥርዓት አንፃር መታየት አለበት ብለዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የፍትሕ ሚኒስትር ተደርገው ሲሾሙ የነበራቸውን የትምህርት ዝግጅት በማየት በፍትሕ ዘርፍ የተሻለ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ እጠብቅ የነበረ ቢሆንም፣ እሳቸው ከመሾማቸው በፊት ከነበሩት ሹመኞች የተለየ ምን አደረጉ? ምን ለውጥ አመጡ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም በሕግ ትምህርት ከአንድ ደረጃውን ከጠበቀ የውጭ ዩኒቨርሲቲ ዶክትሬት ይዘው እንደ መምጣታቸውና የአገሪቱ ትልቅ ተቋም በሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስተምሩ ስለነበሩ ለዚህ አገር ምን ለውጥ አመጡ የሚለውም አልተገመገም ብለዋል፡፡

‹‹እኔ በግሌ ቅሬታ አለኝ፣ ለፍትሕ ሚኒስትርነት ጌዲዮን (ዶ/ር) የዕውቀት ችግር አለባቸው ብዬ አይደለም፡፡ ነገር ግን አፈጻጸማቸውን ካየነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረውን የፍትሕ ጥማት ከማስታገስና ከማርካት ይልቅ፣ አሁንም የፍትሕ ሥርዓቱ የፖለቲካ መሣሪያ እንዲሆን አድርገዋል የሚል ወቀሳ ማቅረብ አፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ከሥልጣን የሚነሱ ሚኒስትሮች ከተሾሙ በኋላ ምን አጉድለው እንደተነሱ፣ ምን ድክመት እንዳሳዩ? ወይም ምን ዓይነት የሥነ ምግባር ጥሰት እንዳሳዩ ሳይቀርብ አዲስ የሚተኩት ሚኒስትሮች ከእነሱ በምን እንደሚሻሉ ሳይነገር ይሾማሉ በማለት፣ ይህንን ከግልጽነትና ከተጠያቂነት መርህ አንፃር የኢትዮጵያ ሕዝብና ምክር ቤቱ ማወቅ የለበትም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በቅርቡ በተደረገው ምርጫ አሸንፈው ፓርላማውን በ2017 ዓ.ም. የተቀላቀሉት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሕዝብ ተወካዮችና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣንና ተግባር ጠቅሰው፣ የተወሰኑት ሚኒስትሮች ከወራት በፊት ተሹመው ወደ ሥራ መግባታቸውና ለፓርላማ በወቅቱ አለመላኩን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ይህ ዓይነቱ አሠራር ምክር ቤቱ ሳያፀድቅና የተሾሙት ቃለ መሃላ ሳይፈጽሙ፣ ወደ ሥራ ማስገባት ሕገ መንግሥቱን መጣስ አይደለም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በክረምት ወቅት የምክር ቤት አባላት ወደ ምርጫ ክልላቸው ተሰማርተው እንደነበር፣ ምክር ቤቱ ከተከፈተ ወዲህ ደግሞ አብዛኛው አባላት የሥልጠና ፕሮግራም ላይ እንደነበሩ፣ እንዲሁም አመራሮች በተመደቡባቸው ቦታዎች ላይ የአመራር ከፍተት ቢፈጠር ከአገር ጥቅምና ከሕዝብ ጥቅም አኳያ አስፈላጊ እንዳልሆነ ታይቶ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመነጋገርና በመግባባት የተሠራ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙትን ጌዲዮን (ዶ/ር) በተመለከተ ስለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፣ እንደ መሪ ፓርቲና እንደ መንግሥት ግምገማ ጌዲዮን (ዶ/ር) በተሰማሩበት በፍትሕ ዘርፍ በጣም ውጤታማ መሆናቸው ተገምግሟል ብለዋል፡፡ ‹‹ዝርዝር ነገር ሳይኖር አጠቃላይና ግምታዊ በሆነ መንገድ መፈረጁ አስቸጋሪ ስለሚሆን ሌላ ጊዜ ዝርዝር ዕውቀት ኖሮን አስተያየት ብንሰጥበት ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለው፣ የፍትሕ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ሰፊ የለውጥ ሥራዎችን ማከናወናቸውንና በዚህ ጅማሮ በፍትሕ ዘርፍ የሚስተዋለው የሕዝብ ጥያቄ በሙሉ ተመልሷል ማለት እንዳልሆነ ግን አስረድተዋል፡፡

Comments

No comments yet. Be the first to leave a comment!

Leave a Comment

Related Posts

Subscribe

You must accept the terms to subscribe.

© Copyright 2025 Addis News. All rights reserved.