A

Addis

ዜና

October 30, 2024

የከተማ መሬት ረቂቅ አዋጅ መሬት ነክ ንብረቶችን ምዝገባ የሚፈቅድ ማሻሻያ ተደርጎበት ቀረበ

Politic

By

ናርዶስ ዮሴፍ

የከተማ መሬት ይዞታ ለመመዝገብ ከአሥር ዓመታት በፊት የፀደቀውን አዋጅ እንዲተካ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የመሬት ነክ ንብረት ምዝገባን የሚፈቅድ፣ እንዲሁም በመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ሒደት ላይ የጊዜ ገደብ የሚያስቀምጥ አንቀጾችን አካቶ ለፓርላማ ቀረበ።

በ2006 ዓ.ም. ፀድቆ በሥራ ላይ የቆየውን አዋጅ ስያሜ ‹‹የከተማ መሬት ይዞታና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ አዋጅ›› በሚል ማሻሻያ ማድረጉን የሚገልጸው ረቂቅ አዋጅ፣ ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ቀርቦ ለከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ እንደሚገልጸው አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅም ሆነ ለማስፈጸሚያነት የወጣው ደንብ በይዞታ ላይ ያለን መብት፣ ግዴታና ኃላፊነት ብቻ አረጋግጦ መመዝገብ እንጂ በይዞታው ላይ ስለሚገኝ መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ እንዲካሄድ አይፈቅድም ነበር።

ማብራሪያው ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዳም፣ ‹‹በቅድሚያ እያንዳንዱን ይዞታ ተቆጥሮና ተመዝግቦ ከተያዘ በኋላ ቋሚ ንብረቱ በቀጣይ ይመዘገባል ከሚል የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ ምክንያት፤›› መሆኑን ይገልጻል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በኢፌዴሪ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 31 ንዑስ አንቀጽ አንድ ፊደል ተራ (ዠ) ላይ፣ ‹የከተማ መሬትና ከመሬት ጋር የተያያዘ ሌላ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ሥርዓት ይዘረጋል፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ መለያ ኮዶች ሥርዓት ያወጣል፣ እንዲሁም የመለያ ኮዶቹ በአገር አቀፍ ደረጃ በከተሞች ተጣጥመው ተፈጻሚ መሆናቸውን ያረጋግጣል› የሚል የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የተሰጠውን ሥልጣን ለመወጣት እንዲያስችል፣ መሬት ነክ ንብረት የሚመዘገብባቸውን ከይዞታ ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ጉዳዮች በረቂቅ አዋጁ እንዲካተቱ መደረጉ ተጠቅሷል።

በዚህም መሠረት የረቂቅ አዋጁ ክፍል ሁለት ‹ስለመሬት ነክ ምዝገባ መሠረቱና አተገባበር› በሚል ሁለት አዳዲስ አንቀጾችን አካትቶ ቀርቧል።

በአንቀጽ ስድስት የመሬት ነክ ንብረት ምዝገባ መሠረቶችን በተመለከተ የተገለጹትም፣ ከመሬት በላይና በታች ያለውን እውነታ የሚያመላክት መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ ቋሚ ንብረት መረጃን ከይዞታው ጋር ተሳስሮ በወረቀትና በዲጂታል ፎርም ከኦርቶ ፎቶ ጋር ተቀናጅቶ እንደሚዘጋጅ ይገልጻል።

የቁራሽ መሬት ማለትም ወሰኑ በምድርና በካርታ ላይ በግልጽ ተለይቶ የመጠቀም መብት የተረጋገጠለት ልዩ የመለያ ኮድ ያለው ነጠላ የመሬት ይዞታ ልዩ መለያ ኮድ፣ ለመሬት ነክ ንብረትም እንደ መለያ ኮድ ሆኖ እንደሚያገለግልም ተደንግጓል።

በዚህ መንገድ ተደራጅቶ በመዝጋቢ ተቋም ውስጥ ተደራጅቶ የሚቀመጠው መረጃ፣ ለንብረት ዋጋ ግምት ዋና ማስረጃ ሆኖ እንደሚያገለግልም ተጠቅሷል።

በረቂቅ አዋጁ ክፍል ሁለት አንቀጽ ሰባት ላይ የመሬት ነክ ምዝገባ አተገባበርን የተመለከቱ ሦስት ድንጋጌዎች ሠፍረዋል።

በእነዚህ ንዑስ አንቀጾች ላይም በመሬት ይዞታ ላይ ወይም በታች ያረፈ መሬት ነክ ንብረት ዝርዝር መረጃ ማለትም የንብረቱ ዓይነት፣ ንብረቱ ያረፈበት ስፋትና ከፍታ፣ ንብረቱ የተገነባበት ጊዜና የቆይታ ጊዜና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን በማረጋገጥ የሚመዘገብ እንደሆነ ያስረዳል።

በተመዘገበ መሬት ነክ ንብረት ላይ የሚከሰቱ ለውጦችና መገለጫዎችም እንደሚመዘገቡ ሲገለጽ ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በይዞታው ላይ ስለሚመዘገብ የመሬት ነክ ንብረትና ዝርዝር ተግባራት ክልሎችና ቻርተር ከተሞች በሚያወጡት ደንብና መመርያ ውስጥ እንደሚገለጽም ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ በመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ሒደት ስለሚታገዱ ጉዳዮች በተመለከተ፣ በቀድሞው አዋጅ ውስጥ የሠፈሩ ድንጋጋጌዎች ላይ በአንቀጽ 16 ሥር ሰፊ ማሻሻያዎችን አድርጓል።

ከእነዚህም መካከል ይዞታ አረጋጋጭ ሹም ማለትም በምዝገባ ተቋሙ ይዞታ ማረጋገጥ ሥራን በበላይነት እንዲመራና እንዲያረጋግጥ የተሾመ ወይም የተመደበ ሰው፣ ‹‹ከመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሠፈር ሥራውን አጠናቆ መውጣት ያለበትን ጊዜ ክልሉ ወይም የከተማ አስተዳደር ይወስናል፤›› በሚል በ2006 ዓ.ም. የሰፈረውን ድንጋጌ ውሳኔው በተጠቀሰው አካላት በኩል የሚደረግ ቢሆንም ነገር ግን የጊዜ ገደቡ ከአምስት ወራት መብለጥ እንደሌለበት ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ በአንድ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሠፈር የመሬት ይዞታን የማረጋገጥ ሒደት መጠናቀቁ ይፋ እስኪደረግ ድረስ፣ የመሬት ይዞታ ስም ዝውውር እንደሚታገድ የሚገልጸው ክፍል ላይ ተጨማሪ ጉዳዮችን አካቷል።

በዚህም መሠረት ረቂቅ አዋጁ ከስም ዝውውር ዕገዳ በተጨማሪ፣ ‹‹መቀላቀልና መክፈል፣ ማንኛውም በይዞታው ላይ ያለን መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት መለወጥ፣ ማስቀረት፣ መቀነስና ማሻሻል የሚችሉ አገልግሎቶች ታግደው ይቆያሉ፤›› ብሏል፡፡

ከእነዚህ ማሻሻያዎች ባሻገር በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በሥራ ላይ ፈጥሯቸዋል ተብለው ከቀረቡ ክፍተቶች መካከል የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ ከመታወጁ በፊት የተሰጡ የፍርድ ቤት ዕግዶች ካሉ የማረጋገጥ ሥራው እንደሚቆም፣ የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ ከታወጀ በኋላ የሚሰጡ ዕግዶች ግን የማረጋገጥ ሥራውን እንደማያስቆሙ የገለጸ በመሆኑ ትግበራ ላይ ትልቅ ችግር የፈጠረ መሆኑ ተገልጿል።

ለመሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዩች ቋሚ ኮሜቴ የተመራው ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 47፣ በፍርድ ቤቶች የሚሰጥ ውሳኔን በተመለከተ ማሻሻያ አድርጓል።

ድንጋጌው በመሬት ይዞታ ላይ የሚገኝ መብት፣ ክልከላና ኃላፊነትን በተመለከተ መብቱን የሚያረጋግጡ፣ የሚያግዱ ፍርዶች፣ ውሳኔዎች ወይም ትዕዛዝ የሚያስተላልፉ፣ የሚለውጡ፣ የሚያስቀሩ ወይም በመዝጋቢው ተቋም ላይ ተጠያቂነት ሊያስከትሉ የሚችሉት ፍርዱ ወይም ውሳኔው ወይም ትዕዛዙ ለመዝጋቢው አካል ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚሆን ያስረዳል።

የከተማ መሬት ይዞታና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በአዋጁ መጠሪያ ስያሜ፣ እንዲሁም በ23 አንቀጾች ላይ ዋና ዋና ማስተካከያዎች በማካተት የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

Comments

No comments yet. Be the first to leave a comment!

Leave a Comment

Related Posts

Subscribe

You must accept the terms to subscribe.

© Copyright 2025 Addis News. All rights reserved.