A

Addis

ዜና

November 06, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራዊ ምክክሩ ለተፋላሚ ወገኖች ከለላ ለመስጠትና የምክክር ውጤቶችን ለመቀበል መስማማታቸው ተገለጸ

Politic

By

ሲሳይ ሳህሉ

ከተቋቋመ ሁለት ዓመታት ሊሞሉት አራት ወራት ያህል ዕድሜ የቀሩት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለተፋላሚ ወገኖች ከለላ ለመስጠት፣ ሕዝበ ውሳኔን ጨምሮ ከሕዝብ የሚመጡ የምክክር ውጤቶችን መንግሥት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መስማማታቸውን አስታወቀ፡፡

ብዙዎች በተስፋና ሥጋት መካከል ባሉበትና ቋጠሮው ባልተፈታ አገራዊ ቁመና ውስጥ ሆኖ ሥራውን ለሁለት ዓመታት ያህል ሲያከናውን የቆየው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣  የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን በተለያዩ ክልሎች እያካሄደ ነው፡፡

የመስፍን ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር) መታሰቢያ ፋውንዴሽን አራተኛ ዓመታዊ ጉባዔውን በማስመልከት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሕግ ባለሙያዎቸና ሌሎችም በተገኙበት በኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ ላይ በማተኮር ‹‹አገራዊ የምክክር ሒደትና በሒደቱ ምን መደረግ አለበት?›› በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት የተገኙት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማርያም የፀጥታ ችግር በዋነኝነት ኮሚሽኑን የፈተነውና ወደኋላ ያዘገየው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹እስካሁን ከመንግሥት ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ አልደረስብንም፤›› ብለዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩ ስለሚያመጣው ውጤት አቀባበል ተፋላሚ ወገኖች ፈቃደኛ ሆነው ለመነጋገርና ለመደራደር ፈቃደኛ ቢሆኑ መንግሥት ምን ያደርጋል በሚል፣   በኮሚሽኑ ግብዣ አማካይነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተገኙበት ምክክር መደረጉን ተናግረዋል፡፡

‹‹የምክክሩ ሒደቱ የሆነ ጊዜ ላይ መጠናቀቁ ስለማይቀር ውጤቱን መንግሥት ካልተቀበለው ከንቱ ነው የሚሆነው፣ ያ ከመሆኑ በፊት የመንግሥታችሁ አቋም ምንድነው ብለን ጠይቀናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በተወካዮቹ አማካይነት የሚያመጣውን ምክረ ሐሳብ ከመተግበር ውጪ የምናደርገው የለም፣ እኛ ከሕዝብ በላይ አይደለንም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ እንኳ የሚጠይቅ ቢሆን ያን የማስፈጸም ግዴታ አለብን የሚል ግልጽ ምላሽ ነው ያገኘነው፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራዊ ምክክሩ መሳተፍ ለሚፈልጉ ተፋላሚዎች ደኅንነት መረጋገጥ መልካም ምላሽ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ ሥራውን ከማንም ጣልቃ ገብነት በፀዳ መንገድ በገለልተኝነተ እየሠራ መሆኑን ቢናገርም የምክክር ሒደቱ ምልዑነት ይጎድለዋል በማለት ምሁራን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ጎራዎች፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች የሚሳተፉ ኃይሎችና በመንግሥት ላይ ያኮረፉ ኃይሎች በምክከር ሒደቱ ላይ ያላቸው ተስፋ እምብዛም እንደሆነ፣ አልፎ አልፎም ሒደቱ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡

በመስፍን ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር) መታሰቢያ ፋውንዴሽን የውይይት መድረክ የተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ በሰጡት አስተያየት፣ የምክክር ኮሚሽኑ በአዋጅ ለሰላም መስፈን እንዲሠራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ሲባል ቢደመምም፣ ወቅታዊ የሆነውን ችግር ለመፍታት ሰላም ሥራ ላይ እየሠራ አይደለም ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ፖለቲካዊ ነው፤›› ያሉት አቶ ደስታ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ለመደራደር ወደ ፕሪቶሪያ እንዲሁም ከኦነግ ሸኔ ጋር ለመነጋገር ወደ ታንዛኒያ ሲሄድ በአገሪቱ ሰላም ለማምጣት የተቋቋመውን የምክክር ኮሚሽንን አለማናገር፣ አለማወያየትና ካለመሳተፍ ባለፈ ኮሚሽኑም ጥያቄ ሲያቀርብ አለመደመጡ የሰላም ሥራውን ጎዶሎ ሊያደርገው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) በመድረኩ ባቀረቡት የመወያያ ሐሳብ፣ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ሊቆጠር ከአራት ወራት በታች የቀሩት ኮሚሽኑ ምክክር በሚለው ትርጓሜ ምክክሩን በመምራት ረገድ በጥሩ መንገድ እየሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ የፖለቲካ ባህል ማልማት የሚል ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት ቢሆንም ምን ዓይነት ስትራቴጂ እንዳለው አለመታወቁን፣ በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መሠረት እንደሚጥልና እንደሚያመቻች ቢቀመጥም ይህን ኃላፊነት ስለመርሳቱ፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ አገራዊ ግንባታ ላይ መሠረት ይጥላል ተብሎ ቢቀመጥም ምክክር ላይ ብቻ መጠመዱን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት መቶ ዓመታት ታሪክ ቤተሰብን ጨምሮ በአገር ውስጥ የሚቋቋሙ ተቋማት በአብዛኛው ሥልጣን የያዘው አካል ማስፈጸሚያ ሆነው እንደሚሠሩ የሚናገሩት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ፣ ‹‹መንግሥት በጣም ጠንካራ ነው፣ ኃይል ያለው ነው፡፡ እንደምታዩት ከተማ አፍርሼ እሠራለሁ የሚል በጣም ጉልበተኛና አቅም ያለው ስለሆነ፣ በየትኛውም ፍልስፍና አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ጨምሮ የምንሠራቸው ተቋማትም ከመንግሥት ነፃ ይሆናሉ ብለን መጠብቅ ያለብን አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡

ዮናስ (ዶ/ር) አክለውም፣ ‹‹አሁን ከመንግሥት ነፃ ናቸው ተብሎ የሚታሰቡት የታጠቁ ኃይሎች ብቻ ናቸው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት እየሞክረ ያለው ዘመናዊነትን ያለ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ አመጣለሁ፣ ልማት አመጣለሁ፣ ሥልጣኔ አመጣለሁ፣ ብልፅግና አመጣለሁ፣ እኔ የምለውን ብቻ ስሙኝ በማለት ተቋማትን በዚህ ዓውድ ብቻ የሚያቋቁማቸው ስለሆነ፣ ኮሚሽኑ ነፃ ነኝ ቢልም የመንግሥት ተቋማት ነፃ ባለመሆናቸው በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት አይኖራቸውም ሲሉም አስረድተዋል፡፡

‹‹የተበላሽ ወይም ጎማው የተነፈሰ የፖለቲካ ሽግግር ላይ በመሆናችን ዜጎች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡ ራሱን ለማግኝትና ተስፋውን ለማለምለም ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ ይሄዳል፤›› ብለዋል፡፡

ምክክሩ በታጠቁ ኃይሎችና በዋልታ ረገጥ ሐሳቦች ውስጥ ሆኖ የሚካሄድ በመሆኑ በቁምነገር የሚወሰድ ሳይሆን፣ መሳቂያ ሆኖ የምክክር ኮሚሽኑን ሥራ ፈተና እንደሚያበዛበት ዮናስ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

‹‹ከማኅበራዊ መስተጋብር አንፃር አገር ቀውስ ውስጥ ሆና ብዙ ሰው ሞቷል፣ አሁንም እየሞተ ነው፣ በዚህ ሒደት ወደ ምክክር ከመገባቱ ቀድሞ ሁሉም ለሐዘን መቀመጥና ድንኳን መጣል ነበረበት፤›› ያሉት ዮናስ (ዶ/ር)፣ በአማራ ክልል ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በባህር ዳር አካባቢ ገበሬዎች ማዳበሪያ ስጡን በማለት ጅራፍ ይዘው ሰላማዊ ሠልፍ ወጥተው በመንግሥት አለመሰማታቸው፣ በሰላሌ የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት ወጥተውና ልጆች ሞፈር ተሽክመው አደባባይ ወጥተው አለመሰማታቸው የማኅበረሰቡ የኖረ አገር በቀል እሴትና ባህል ከዘመናዊው ዕሳቤ ጋር ተጣጥሞ መሄድ አለመቻሉ ነው፤›› በማለት አስድተዋል፡፡

‹‹ማኅበረሰቡ ስለሰላም መናገር የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ ማረስ አልቻልኩም፣ እባካችሁ የምትዋጉና የምትገዳደሉ አቁሙና ጊዜ ስጡኝ ልረስ የሚል የማኅበረሰብ ሰዋሰው እየሰማን፣ በዚህ ምኅዳር ውስጥ እነዚህን ማኅበራዊ አገር በቀል እሴቶችን  ሳያካትቱ የሚደረገው ዘመናዊ የምክክር ሒደት ውጤታማነት ሰላምና ማኅበራዊ ትስስር ያመጣል ብሎ መጠበቅ ይከብዳል፤›› ሲሉም አክለው ገልጸዋል፡፡

ዮናስ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የምክክር ኮሚሽኑ ማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉ አገር በቀል እሴቶች፣ በአገር ሰላም ላይ ለመሥራት ከተቋቋሙ ተቋማት፣ ከሽግግር ፍትሕ፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከቀደሙ ልምዶች፣ ለሰላም ተሠርተው ከፈረሱ ተቋማት፣ ከመልሶ መቋቋም ኮሚሽን ጋር አብሮ ሲሠራና ለመሥራት ሲንቀሳቀስ አልታየም፡፡

በደቡብ  አፍሪካ ፕሪቶሪያና በታንዛኒያም ሆነ በሌሎች በተሞከሩ የሰላም ጥረቶች ኮሚሽኑ አለመሳተፉ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሰላም ጥረቶች የተፈረካከሱ መሆናቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት በአስተዳደራዊ መንገድ ለመፍታት የሚሞክራቸውና ሌላ ቁስል እየፈጠሩ ያሉ ጉዳዮች ያሏቸው ሰዎችን ማፈናቀል፣ ክልል ማዋቀር፣ ከተማን አፍርሶ መሥራት፣ 12ኛ ክፍል የጨረሰን ተማሪ ዩኒቨርሲቲ እንዳይገባ መገደብና ሌሎችንም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ያኮረፉና ተስፋ የቆረጡ በርካታ ወጣቶች የሚሄዱበት ሲያጡ መሣሪያ ገዝተው ለመዋጋት በሚያስቡባት አገር ምክክሩ የሚኖረው ሚና ውስን በመሆኑ፣ መጀመሪያ የሰላም ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ያስፈልግ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ዮናስ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የፖለቲካ አመራሩ ፀር ምሁራዊ አስተያየቶች መስጠት እየለመደ ነው፡፡

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽነሩ መላኩ ወልደ ማርያም በበኩላቸው፣ የአገረ መንግሥት ግንባታ በ11 ኮሚሽነሮችና በጥቂት ሰዎች የሚከናወን አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ኮሚሽኑ ከሕዝብ የመጣውን ሐሳብ ሰንዶ እንደሚያቀርብና በምክክር ሒደቱ ጠያቂ ማኅበረሰብ ይፈጠራል ብለው እንደሚምኑ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኮሚሽን ነው፣ ገንቢ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በዚህ አገር የሚቋቋሙ ተቋማት በሙሉ ሁልጊዜም ወቀሳና ስድብ ሲደርስባቸው ነው የሚታየው፣ ይህ እንደ አንድ ባህል ተወስዷል፡፡ ኮሚሽኑ ገለልተኝነቱና ነፃነቱ ጥያቄ  ውስጥ ከገባ በማስረጃ ተደግፎ መቅረብ አለበት፡፡ በማስረጃ ተደግፎ የቀረበ ነገር ግን የለም፣ የሚሰጡ አስተያያቶች ገንቢ እንጂ አፍራሽ መሆን የለባችውም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኮሚሽናችን አቋም የሽግግር ፍትሕና የአገራዊ ምክክር ውጤት ነው፡፡ የሽግግር ፍትሕ ከአገራዊ ምክክር ጋር አብሮ ጎን ለጎን የሚሄድ ባለመሆኑ፣ ተበዳይ በምክክር ነው የሚገኘው፤›› በማለት ምክክሩ መቅደም እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

‹‹ውጤታማ ይሆናል አይሆንም የሚለው ጉዳይ በሒደት የሚታይ ሆኖ፣ ኦነግ ሽኔንም ሆነ ፋኖን የማነጋገር ጉዳይ በራሳችን፣ በሌሎች ሰዎችና በሦስተኛ ወገን በኩል እየሄደንበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የፀጥታው ሁኔታ የተስተካከለ ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ጊዜ አንፈጅም ነበር፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ሕዝቡ ሒደቱንም ውጤቱንም በባለቤትነት ይያዘው፣ ይህች አገር የሁላችንም ናት፣ ሰው የሚፈለገው ለጦርነት ብቻ መሆን የለበትም፤ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Comments

No comments yet. Be the first to leave a comment!

Leave a Comment

Related Posts

Subscribe

You must accept the terms to subscribe.

© Copyright 2025 Addis News. All rights reserved.